በኮምፒዩተር ጥገና አገልግሎት የሰለጠኑ ስራ ፈለጊ ወጣቶች ስልጠናው የመስራት አቅም እንደፈጠረላቸው ገለጹ፡፡
  February 15, 2021    News

ከኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት በዝንባሌያቸው ተመልምለው በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኮምፒዩትር ጥገና አገልግሎት ለአስራ አምስት ቀናት ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩት አስራ አምስት ስራ ፈላጊ ወጣቶች ከስልጠናው ያገኙትን ፋይዳ አስረድተዋል፡፡ ወጣት አስራር መሃመድ ከስልጠናው ያገኘውን ጥቅም ሲገልጽ በኮምፒዩተር ጥገና እና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ አስፈላጊውን እውቀትና ክህሎት በመጨበጤ በመንግስት እና ግል ተቋማት ተቀጥሮ የመስራት እድል ባላገኝ እንኳን ከስልጠናው በግል መስራት የምችልበትን አቅም ፈጥሬያለሁ ብሏል፡፡ ሌላኛዋ ሰልጣኝ ኤልሃም ሁሴን በበኩሏ ስልጠናው በተማረችበት መስክ መሰጠቱ ይበልጥ ተነሳሽነቷን እንደጨመረላት ገልጻ ከስልጠናው ባገኘቸው ግንዛቤና ክህሎት ከሌሎች ጋር በማህበር ተደራጅታ ስራ ፈጥራ ለመሰማራት ያላትን ቁርጠኝነት አንጸባርቃለች፡፡ በቅድሚያ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በማህበረሰብ አገልግሎት መስክ ተቋማዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ስለሚገኝ ምስጋና ሊቸረው ይገባል ያለው ላመስግን ምህረት ስልጠናውን ለረጅም ጊዜ ሲመኘው እንደነበር ገልጾ በቀጣይ በተሟላ መንገድ ወደ ስራ እንድንገባ ተቋሙ የኔትወርክ ዝርጋታ ስልጠና ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጾ ከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ አስፈላጊውን ብድርና መስሪያ ቦታ ሊያመቻችልን ይገባል ብሏል፡፡ ሌሎች ያነጋገርናቸው ስራ ፈላጊ ወጣቶችም ስልጠናው የመስራት አቅም እንደፈጠረላቸው የገለጹ ሲሆን በቀጣይ በልብስ ስፌት የሰለጠኑ ወጣቶች ከስልጠናው ያገኙትን ፋይዳ ይዘን እንደምንቀርብ ከወዲሁ መግለጽ እንወዳለን፡፡