የመንግስት አገልግሎት ዘርፍ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታና የማስተግበሪያ ሰነድ ላይ ስልጠና ተሰጠ፡፡
  February 10, 2021    News

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የመንግስት አገልግሎት ዘርፍ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታና የማስተግበሪያ ሰነድ ላይ ያተኮረ ስልጠና የካቲት 02/ 2013 ዓ.ም በወሎ ዩኒቨርሲቲ ደሴ ካምፓስ ተሰጠ። ስልጠናውን የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አፀደ ተፈራ የመክፈቻ ንግግር አድርገው የከፈቱት ሲሆን ከሁለቱም ካምፓስ የተውጣጡ ዳይሬክተሮች፣ ቡድን መሪዎች እና የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል። ዶ/ር አፀደ በመክፈቻ ንግግራቸው ስልጠናውን አስመልከተው እንደተናገሩት፣ “የመንግስት አገልግሎት ዘርፍ ዜጎች የሚጠብቁትን አገልግሎት በብቃት መስጠት እንዲችል ከጊዜና ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የተናበበ የለውጥ መርሃግብሮችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል” ካሉ በኋላ የፍኖተ ካርታው ሰነድ መዳረሻ ግብ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ማረጋገጥ፣ የፌደራል መንግስት አስተዳደር ሥርዓትን ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ማድረግ፣ በሁሉም የዕድገት መለኪያ መስፈርቶች ሃገራዊ እሴትን ማሳደግ እና በስራ አመራር ስልቱ የመንግስት ስራ ከፖለቲካ ፓርቲ አሰራር ጋር የማይደበላለቅበት፣ ነገር ግን ሁለቱም ተናበው የዜጎችን እርካታ ማረጋገጥ የሚቻልበት እንዲሆን ነው ብለዋል። ስልጠናውን የሰጡት የሰው ሃብት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ በዕደማርያም አካሉ እና የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር ወ/ሮ ዘቢባ መሀመድ ሲሆኑ ይህን የአስር አመት ፍኖተ ካርታ የፌደራል ሲቪል ሰርቪ የላከው የመንግስት ተቋማት ከሰነዱ ጋር ትውውቅ እንዲያደርጉ እንጂ የአፈፃፀምና አተገባበር መመሪያዎቹ ገና አልተላኩም፤ ወደፊት ይላካሉ ብለዋል። ፍኖተ ካርታው በስልጠናው ላይ ሲብራራ እንደተገለፀው አዲሱ የ10 አመት እቅድ ከመመሪያና ፅንፀሀሳብ ይልቅ ተግባራዊ አፈፃፀም፣ ብቃትና ጥራት ላይ የሚያተኩር ይሆናል ተብሏል። በተለይ ደግሞ የመንግስት አገልግሎት ዘርፍ ከፖለቲካ አሰራር ነፃ እና ገለልተኛ መሆን እንዳለበትና አንድ ሰራተኛ ብቃትና ችሎታውን በተግባር የሚያሳይበት አቅሙ እሳከለው ድረስ "ዘሎ ማለፍ" ማለትም መመሪያዎች የሚጠይቁት የስራ ልምድ ወይም ሌሎች የፅንሰሃሳብ ክልከላዎች ሳይገድቡት የሚፈለገው ሙያና የስራ ኃላፊነት ላይ ተመድቦ ህዝብና ሃገርን ሊያገለግል የሚችልበት አሰራር እንደሚዘረጋ አፅንዖት ተሰጥቶታል። በቀረበው ፍኖተ ካርታ ላይ በአሰልጣኞቹ አወያይነት ተሳታፊዎች አስተያየት እንዲሰጡበት የተደረገ ሲሆን ሰነዱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብሎም እንደ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሊኖረው የሚችለው መልካም እድል እና ስጋቶች ተነስተው እንደ ግብዓት መወሰዳቸው ተገልፆ ስልጠናው ተጠናቋል።