ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ህንድ የጋራ ግንኙነትን አስመልክቶ ሴሚናር አካሄደ፡፡
  July 26, 2021    News

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያና ህንድ መካከል የሁለትዮሽ ግንኙነትን አስመልክቶ ሴሚናር አካሂዷል፡፡ በሴሚናሩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መላኩ ታመነ እና እሳቸውን ተከትሎ ንግግር ያደረጉት የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶ/ር ኢንጂነር ከማል መሃመድ ስለ ኢትዮጵያና ህንድ ታሪካዊ ግንኙነትና ሁለቱም ለነጻነት ስለከፈሉት ዋጋ ትኩረት ሰጥተው ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የዩኒቨርሰቲ፣ ቴክኒክና ሙያ፣ ኢንስቲትዩትና ኢንዱስትሪ ትስስር አስተባባሪ የሆኑት አቶ ፋሲል አለማዬሁ ስለ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ዳራ አጠቃላይ ዳሰሳ በማድረግ በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምህንድስና እና ቴክኖሎጂ ኮሌጆች ስር በሚገኙ ትምህርት ክፍሎች የተፈጸሙ ተግባራት ገለጻ አቅርበዋል፡፡ አቶ ፋሲል በወቅቱ የዩኒቨርሲቲውን ገጽታ የሚዳስስ ምስል ያሳዩ ሲሆን ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ህንድ አገር ከሚገኙ ተቋማት ጋር የህብረት ስምምነት ሰነድ ከመፈራረም ባሻገር በብይነ መረብ ኮንፈረንስ እንዲሁም ወርክ ሾፕ እና ስልጠና በማካሄድ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር መደረጉን በማስታወስ በተቋሙ የሚገኙ የህንድ መምህራንም ተሳትፎን አብራረተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ምክትል ጸሃፊ የሆኑት የተከበሩ ሁሴን በህንድ ስላለው ብዝሃ ብሄር፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ የሀይማኖት ነጻነትና በልዩነት ስላለው አንድነት ገለጸው ህንድ በኢትዮጵያ በቴክስታይል፣ ፋርማሲ፣ አውቶሞቢል፣ ጤና፣ ትምህርት እና ንግድ ሴክተር ግዙፍ ኢኮኖሚን እንደምታንቀሳቅስ መረጃ ሰጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር የተከበሩ ሽሪ ሮበርት ሸትኪንቶንግ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንደጎበኙ ገልጸው ትምህርት በጋራ ግንኙነት ወቅት ከሚያስተሳስሩ ዋነኛ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ አምባሳደሩ በተቋሙ የሚያስተምሩ የህንድ መምህራን በትምህርት መስክ ከሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ባሻገር የማህበረሰቡን ችግር መፍታት እንደሚገባቸው አሳስበው በዚህ ረገድ እንደ ተሞክሮ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላትና ለተሰራው ስራ እውቅና በመስጠት በሚቀጥለው አመት ለሶስት ወይም አራት መምህራን በህንድ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የትምህርት እድል እንደሚመቻች ቃል ገብተዋል፡፡ የአገራቱና የተቋማቱ ግንኙነት በተለያዬ መስክ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በተገለጸበት በዚህ ሴሚናር መጭረሻ በተያዘው ፕሮግራም መሰረት አምባሳደሩን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ታዳሚዎች በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ግቢና በጥቁር አባይ ኮንዶሚኒዬም ተገኝተው አረንጓዴ አሻራ አስቀምጠዋል፡፡