ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከቤዛ ፖስትሪቲ ጋር በመተባበር በጫማ ማስዋብ ስራ ለተሰማሩ ወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ስልጠና እንዲሰጥ እያደረገ ነው፡፡
  July 26, 2021    News

በማህበረሰብ አገልግሎት መስክ ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የስልጠና እና መሰል ድጋፎችን እያደረገ የሚገኘው ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኮምቦልቻ ከተማ የተለያዩ ቀበሌዎች በጫማ ማስዋብ ስራ ላይ ለተሰማሩ መጣቶች የህይወት ክህሎትና ስራ ፈጠራ ስልጠና እንዲሰጥ እያደረገ ነው፡፡ በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አሳምን አያሌው በመክፈቻ ንግግራቸው በኮምቦልቻ ከተማ የተለያዩ ቀበሌዎች ደጋፊ ለሌላቸውና በጫማ ማስዋብ ስራ ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት በተመረጡ ቦታዎች ላይ ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው የመስሪያ ሸድ ተጠቅመው የተሻለ ገቢ መፍጠር እንዲችሉ ስልጠናው የስራ ተነሳሽነትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡ በኮምቦልቻ ቤዛ ፖስትሪቲ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የማህበረ-ኢኮኖሚ ዘርፍ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መኳንንት ወርቅዬ በበኩላቸው ከስልጠናው በሁዋላ በእነሱ ተቋም ለስራው የሚያስፈልጉና ተጨማሪ ግብዓቶች እንደሚሟሉ ገልጸው ወደ ስራ ሲገቡ የቁጠባን ባህል ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸውም ገልጸዋል፡፡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህራን እና በመስኩ የረጅም ጊዜ የማሰልጠን ልምድ ያካበቱት አሰልጣኝ ያሲን መሃመድ እና ሰይፈ ቸኮል ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በህይወት ክህሎት ዙሪያ ስልጠና እንደሚሰጡ የተገለጸ ሲሆን በሶስተኛው ቀን እንዲሁ በስራ እድል ፈጠራ ዙሪያ ተጨማሪ ስልጠና እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡