ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በጥናትና ምርምር ስነ-ዘዴና አተገባበር ዙሪያ ለመምህራን ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው፡፡
  January 30, 2021    News

ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በጥናትና ምርምር ስነ-ዘዴና አተገባበር ዙሪያ ለመምህራን ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው፡፡ ========================================== በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሪሰርች፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ጽ/ቤት አስተባባሪነት የተዘጋጀው ይህ ስልጠና የመምህራንን የጥናትና ምርምር ክህሎት ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መላኩ ታመነ በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ምርምር ማካሄድ ዩኒቨርሲቲዎች በአዋጅ ከተቋቋሙበት ዋነኛ ተግባር አንዱ መሆኑን አስታውሰው መማር ማስተማር በጥናትና ምርምር አስካልታገዘ ድረስ የሚጠበቀውን ውጤት ማስመዝገብ አይቻልም ብለዋል፡፡ ዶ/ር መላኩ አይዘው ችግር የሚፈታው እውቀትን ተግባር ላይ በማዋል በመሆኑ መምህራን ጥናትና ምርምር በማካሄድ የማህበረሰቡን ችግር መፍታት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ የጥናትና ምርምር ወረቀት ማዘጋጀት የመስሪያ በጀት ለማግኘት ወሳኝ ሚና ይጫወታል የሚሉት ዶ/ር መላኩ መምህራኑ ይህን ግብ ለማሳካት በግላቸው ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር ለስልጠናው ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡ በእለቱ በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ዶ/ር አሉላ ተሰማ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት አመራር እና አስተዳደር ረዳት ፕሮፌሰር በበኩላቸው በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ያላቸውን የረጅም አመታት የማስተማርና ምርምር ተሞክሮ ለታዳሚዎች በማጋራት የማነቃቂያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በቴክኖሎጂ ዘመን ምርምርና ፈጠራ የችግሮች ሁሉ መፍቻ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአህጉርና አለም አቀፍ ደረጃ በሲቪልና ኮንስትራክሽን ምህንድስና መስክ በማስተማር፣ በማማከርና ምርምር በማካሄድ እውቅናን ያተረፉትና ስልጠናውን ለማካሄድ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ፕሮፌሰር አበበ ድንቁ በትምህርት ሙያዊ ስነ-ምግባር፣ በጥናትና ምርምር ምንነትና አስፈላጊነት፣ አይነት፣ በርዕስ አመራረጥ፣ በምርምር ጽሁፍ አዘገጃጀትና አተገባበር፣ በበጀት አፈላለግና ህትመት እንዲሁም በውጭ አገር የትምህርት እድል ዙሪያ ስልጠና በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን መምህራኑም ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት በውይይት እያዳበሩት ይገኛሉ፡፡