ኢንስቲትዩቱ በከፍታ ፕሮጀክት ድጋፍ ለ12 ኛ ክፍል ተማሪዎች የፈተና ዝግጅት እና የትምህርት ውጤታማነት ላይ የማነቃቂያ ስልጠና ሰጠ።

ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 04/01/2015 ዓ.ም

በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የከፍታ ፕሮጀክት ድጋፍ አስተባባሪ በሆነው የሙያ ልማት ማጎልበትና የስራ ፈጠራ ማዕከል አመቻችነት ኮምቦልቻ ከተማ ለሚገኙ አጠ/2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የ12 ኛ ክፍል ማትሪክ ተፈታኝ ተማሪዎች የማነቃቂያ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሜካኒካል ምህንድስና መምህር እና የሙያ ልማት ማጎልበትና የስራ ፈጠራ ማዕከል አስተባባሪ ዉብእሸት ደግፌ (ረ/ፕ) በመክፈቻ ንግግራቸው ከፍታ ፕሮጀክት ወጣቶችን ስራ ፈጣሪ በማድረግ ረገድ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በማስተዋወቅ ኢንስቲትዩቱ በከተማዋ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች አብሮ በመስራት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

መምህር ዉብእሸት ተማሪዎች ከዘልማዳዊ ሃሳብ ማነቆ ተላቀው ወደ ሚፈልጉት ግብ ለመድረስ የእችላለሁ አስተሳሰብ እና ጥረትን ሊላበሱ እንደሚገባ የማነቃቂያ ንግግር አድርገዋል፡፡

በማሰልጠን ረጅም ልምድ ያካበቱት የኢንስቲትዩቱ የተማሪዎች ጋይዳንስና ካውንስለር የስነ-አዕምሮና ሳይኮሎጂ ባለሙያ እንዲሁም የስብዕና ግንባታ አሰልጣኝ አቶ አልዩ እንድሬ እና በቴክስታይል ምህንድስና መምህርና በ አይ ኦ ቲ የማሰልጠን ብቃት እውቅና ያላቸው የህይወት ክህሎት አሰልጣኝ አቶ ሰይድ ሽፈራው ተማሪዎች ለማትሪክ ፈተና በቀራቸው ጊዜ እንዴት ውጤታማ ዝግጅት ማድረግ እንደሚችሉ እና በቀሪ ዘመናቸው ሊተገብሯቸው የሚገቡ የህይወት ክህሎቶች ላይ የማነቃቂያ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በስልጠናው ውጤታማ የአጠናን ዘዴ፣ የጊዜ አጠቃቀም፣ ግብ የማስቀመጥ መርሆ፣ ትኩረትን መላበስ፣ የአቻ ግፊትን መቋቋም፣ ከሱስ ራስን መጠበቅ እና የፈተና ውጥረትን መቀነስ፣ ለማትሪክ ፈተና የሚደረግ የስነ-ልቦና እና ስልታዊ የዝግጅት ምዕራፍ እና መሰል ርዕሰ ጉዳዮች ተዳሰዋል፡፡

ስልጠና የተሰጠባቸው የቢራሮ፣ ሚሊኒየም እና ኮምቦልቻ አጠ/2ኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሳነ መምህራን ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው እንዲህ አይነቱ ስልጠና ተማሪዎች የራስ መተማመን አቅማቸውን በማሳደግ የሚገጥሟቸው ፈተናዎችን ለማለፍ እንዲችሉ ግንዛቤን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

Scroll to Top