ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲዩት 19/01/2015 ዓ.ም
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አለሙ ስሜ በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲዩት ተገኝተው ከወረራ በኋላ በመልሶ ግንባታ የተሰሩ እና በመሰራት ላይ የሚገኙ ቢሮዎችን፣ወርክሾፖችን፣ላቦራቶሪዎችን እና የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዝግጅት ሁኔታን ጎብኝተዋል።
እንድሁም የቦርድ ሰብሳቢው በመገንባት ላይ የሚገኘውን አዲሱን ቤተ-መጽሃፍት እና የግቢ ማስዋብ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል፡፡
በተጨማሪም የቦርዱ ሰብሳቢው መድረኩን በመሩት ውይይት ላይ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ ከጦርነቱ በኋላ በተቋሙ የተከናወኑ የ2014 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም ሪፖርትን ያቀረቡ ሲሆን የተሰሩ አበይት ጉዳዮችንም አቅርበዋል፡፡
ሪፖርቱ ተቋሙን መልሶ ከመገንባት አኳያ የሃብት ማፈላለግ እና የተሰሩ የጥገና ሰራዎችን የዳሰሰ ሲሆን በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት መስክም ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በትስስር የተሰሩ ስራዎችን አካቷል፡፡
ዶ/ር መንገሻ አያይዘው የ2015 ዓ.ም እቅድንም ያቀረቡ ሲሆን የቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራትን በመግለጽ በበጀት አመቱ ጸድቀው ወደ ስራ የሚገቡ ፕሮጀክቶችንም አስተዋውቀዋል፡፡
ሪፖርቱና እቅዱ ከቀረበ በሁኋላ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የቦርዱ ሰብሳቢ ተቋሙ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት እና ተወዳዳሪ ለመሆን የጀመረውን ጥሩ አፈጻጸም አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡