የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ የሶፍት ዌር ምህንድስና ትምህርት ክፍል ለደቡብ ወሎ ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ የዞኑን መረጃዎች ለማስተዋወቅና ገጽታን ለመገንባት የሚያግዝ ድህረ ገጽ ሰርቶ አስረከበ፡፡
በወቅቱ በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሶፍት ዌር ምህንድስና መምህርና ድህር ገጹን ካበለጸጉት ሶስት ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ገብረመድህን መኮነን ስለ ድህረ ገጹ አስፈላጊነት እና ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ድህረ ገጹ ልዩ የተቋሙ ትክክለኛ አድራሻ በመሆኑ በሌሎች አካላት ተመሳስሎ ከሚሰራ ሃሰተኛ አድራሻ ስጋት ነጻ ነው ብለዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ሰይድ አህመድ በበኩላቸው አይ ሲ ቲ የቀጣይ አገሪቱ ልማት እድገት አንዱ ግብ በመሆኑ ቴክኖሎጂው መረጃን በቀላሉ በፍጥነት እና በጥራት ተደራሽ ለማድረግና የዞኑን ገጽታ ለመገንባት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርላቸው ገልጸው ወሎ ዩኒቨርሲቲ በዞኑ የመጀመሪያው ድህረ ገጽ ያበለጸገ ተቋም እንዲሆኑ ከማስቻሉም በተጨማሪ በነጻ ያበለጸገላቸው ይህ ድህረ ገጽ ግማሽ ሚሊዮን ብር ወጭ ይጠይቅ እንደነበር አሳውቀዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ድህረ ገጹን በነጻ ለሰሩለት ለመ/ር ገብረመድህን መኮነን፣ ለመ/ር መከተ ተድላው እና ለተማሪ ዳንዔል ጌታዬ የእውቅና ሰርቲፊኬት ያበረከተ ሲሆን ወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢው ችግር ለመፍታት እያደረገ ላለው የማህበረሰብ አገልግሎት ስራ የምስጋናና የእውቅና ሰርቲፊኬት ሰጥቷል፡፡
የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አሳምን አያሌው ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛው የመማር ማስተማር ስራው በተጨማሪ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ የተለያዩ ችግር ፈች ጥናትና ምርምር በማካሄድ የማህበረሰቡን ችግር እየፈታ እንደሚገኝ አስታውሰው ይህ የድህረ ገጽ ብልጽግናም የዚህ አንድ ማሳያ ነው ብለዋል