ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከ Habhab for society team ጋር በመተባበር በቴክኖሎጂ መስክ ለወራት ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ፡፡

ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የአብ ፋክተሪ አካዳሚ ተማሪዎች ከሌሎች ሃገራት ከሚገኙ አካላት ጋር በጥምረት ከመሰረቱት Habhab for society team ጋር በመተባበር ለሶስት ወራት ቅዳሜና እሁድ በፕሮግራሚንግ፣ ኤ አይ ሮቢቲክስ፣ ጤናማ የአኗኗር ስነ ዘዴ እና አመራር ክህሎት ላይ ያሰለጠናቸውን ስድስት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡

የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ዲን አቶ መልካሙ ጸጋዬ ስልጠናው ከኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ጋር በትብብር እንደተሰጠ ገልጸው ይህም ከመደበኛ የመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ ከሚሰራቸው የማህበረሰብ አገልጎሎት ተግባራት መካከል አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

አቶ መልካሙ አሁን ከተሰጠው መሰረታዊ የኮምፒዩተር ፕሮግራሚንግ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጄንስ፣ ጤናማ አመጋገብ እና የህይወት ክፍሎት ስልጠና በተጨማሪ በቀጣይም በእኝህ እና ሌሎች መስኮች ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ተመሳሳይ ስልጠና እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል፡፡

የስልጠናው አስተባባሪ የሆነችው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምሩቅ እና በአፕ ፋክተሪ አካዳሚ እየተማረች የምትገኘው ሃያት ጋሻው Habhab for society team በአፕ ፋክተሪ አካዳሚ ተማሪዎችና ሌሎች አገራት ከሚገኙ ሰዎች ጋር በቅንጅት ተመስርቶ ዩቲዩብ ቻናል በመክፈት በጤናማ የህይወት አኗኗር ላይ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጻ በዚያ ተደራሽ ለማይሆኑ አካላት ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም እንደሚሰሩ ተናግራለች፡፡

አሁን የሚያሰለጥኑበት ፕሮግራም Habhab for kids እንደሚባል የጠቆመችው አሰልጣኟ በፕሮግራሚንግ፣ በኤ አይ ሮቦቲክስ፣ በዌብ ዴቭሎፕመንት እና በጤናማ የአኗኗር ስልት ዙሪያ ስልጠና ተሰው ለማስመረቀቅ እንደበቁ ገልጻለች፡፡

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ተማሪዎች በስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ምስለ ትዕይንት ለታዳሚዎች ያቀረቡ ሲሆን ልዩ ልዩ የሮቦቲክስና አርቴፊሻል ኢንተለጄንስ ቴክኖሎጂ እና ወደ ፊት ሊሰሩዋቸው ያሰቧቸውን ሌሎች የፈጠራ ስራዎችንም ጭምር ገለጻ አቅርበዋል፡፡

በዝግጅቱ መጨረሻ ላይ ተጋባዥ እንግዶች ንግግር ያደረጉ ሲሆን ተመራቂዎችም ሰርቲፊኬትና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

Scroll to Top