ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 13/01/2015 ዓ.ም (ህዝብ ግንኙነት)
ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኮምቦልቻ ሪጆ ፖሊታን ከተማ አስተዳደር ስር ላሉ የክፍለ ከተማ አና የቀበሌ አስተዳደር አመራሮች አንዲሁም የወሳኝ ኩነት ባለሙያዎች በአገልግሎት አሰጣጥና መረጃ አያያዝ ዙሪያ ስልጠና እንዲሰጥ አድርጓል፡፡
የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መላኩ ታመነ አለም ወደ አንድ መንደር በተቀየረችበት በዚህ ዘመን ተወዳዳሪ ለመሆን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና የመረጃ አያያዝ ስርዓት ዘመናዊ መሆን እንዳለበት አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አሰራሩን ዘመናዊ በማድረግ ፈጣንና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ የቴክኖሎጂ እና ምርምር ውጤቶችን በመጠቀም ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ዶ/ር መላኩ የአሰራር ስርዓቱን ለሌሎች ተደራሽ ለማድረግም የተጀማመሩ ሙከራዎች እንዳሉ አብራርተዋል፡፡
የኮምቦልቻ ሪጆ ፖሊታን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሃመድ አሚን በበኩላቸው ስልጠናውን ላዘጋጁት አካላት እውቅና ሰጥተው አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዳሉ በማውሳት በቴክኖሎጂ የተቃኘ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የደንበኛ ርካታን መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡
ጥራት ያለው አገልግሎት እና የተደራጀ መረጃ አያያዝ የተገልጋዩን አመኔታ ከማጎናጸፉ ባሻገር ደንበኛን ለመሳብና ኢንፈስትመንትን ለማስፋፋት ጭምር ያለውን ፋይዳ በተጨባጭ ምሳሌ ተሞክሮን አጋርተዋል፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኔጅመንት መምህር የሆኑት ሙሉጌታ ጫኔ (ረ/ፕ) የአገልግሎት አሰጣጥና ደንበኛ አያያዝ ዘዴ በሚል ርዕስ ስልጠና የሰጡ ሲሆን በኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ የኢንፎርሜሽን ሲስተም መምህር የሆኑት አቶ ታደሰ ቢራራ ደግሞ ስለ አስተዳደራዊ መረጃ አያያዝ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡
በተያያዘ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ዘርፍ መምህር የሆኑት ደሳለኝ ተስፋው (ረ/ፕ) ስለ ወሳኝ ኩነት ምንነት አጠር ያለ ስልጠና የሰጡ ሲሆን ቤዛ ፖስትሪቲ ልማት ድርጅትም ያደረገውን የስራ እንቅስቃሴ አቅርቧል፡፡
የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምር፣ ማህበረሰብ ጉድኝትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምን አያሌው ዘመኑ የተማረ፣ ቁርጠኛ፣ ከሁኔታ ጋር ራሱን የሚያላምድ፣ ተግቶ የሚሰራ፣ መረጃ ላይ ተመስርቶ ውሳኔ የሚያስተላልፍ መሪን እንደሚጠይቅ ገልጸው ስልጠናው የአመለካከትን ለውጥ እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት አንጸባርቀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ዶ/ር አሳምን በቀጣይም በተመረጡ እና ችግር ፈች በሆኑ ጉዳዮች ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና እና ድጋፍ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ስልጠናውን ለተካፈሉ የልዩ ልዩ አደረጃጀት አመራሮች የእውቅና ሰርቲፊኬት ተሰጥቷቸዋል፡