ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 10/12/2014 አ.ም. ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በእንጨትና ብረታ ብረት ስራ ህብረት ሽርክና ማህበር ለተደራጁ ስምንት ኢንተርፕራይዞች ያገለገሉ ብረታ ብረትና ጣውላዎች ድጋፍ አድርጓል::
የድጋፍ እርክክቡ በተደረገበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር መላኩ ታመነ ዛሬ የተደረገው መጠነኛ ድጋፍ ተጫባጭ ለውጥ ካመጣ በቀጣይም እገዛው ይቀጥላል ያሉት ዶ/ር መላኩ ለዚህም ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል::
ዶ/ር መላኩ የእንጨት እና ብረታ ብረት ዘርፍ አዋጭ የስራ መስክ መሆኑን በመጠቆም ማህበራቱ በቀጣይ ለትላልቅ ተቋማት ምርት በማቅረብ ትርፋማ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት በማንጸባረቅ ተቋሙ የሚያደርገው የእቀትና ክህሎት ድጋፍ እና ስልጠና ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል::
የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምር፣ ማህብረሰብ ጉድኝትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ዶ/ር አሳምን አያሌው በበኩላቸው መህበረሰብ አገልግሎት አንዱ የዩኒቨርሲቲው ተልእኮ መሆኑን በማስታወስ ዛሬ የተደረገው የብራታ ብረት እና ጣውላ ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን ከ ግማሽ ሚሊየን ብር በላይ እንደሚያወጣ አሳውቀዋል:: ዶ/ር አሳምን ኢንተርፕራይዞቹ የተደረገላቸውን ድጋፍ በመጠቀም የላቀ ውጤት ሊያስመዘግቡ እንደሚገባ በማስገንዘብ ኢንስቲትዩቱ የስራ እንቅስቃሴያቸውን በቅርበት በመከታተል ተጨማሪ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ እገዛ ያደርጋል ብለዋል:: የ ኮ/ቴ/ኢ የ ምክትል ማኔጅንግ ዳይሬክተር አዲሱ ሀይሌ ( ረ/ፕ) በበኩላቸው ኢንተርፕራይዞቹ የግብአት እጥረት ሊኖርባቸው እንደሚችል ግምት ውስጥ አስገብተው ድጋፉን በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ አሳስበው ተቋሙ ለሌሎች ኢንተርፕራይዞች በግቢው ውስጥ ስራ መፍጠሩንም መረጃ ሰጥተዋል::
የኮምቦልቻ ሪጆ ፖሊታን ከተማ አስተዳደር የስራ እና ስልጠና መምሪያ ሃላፊ የሆኑት አቶ አብዱ ቸሩ ስምንቱ ኢንተርፕራይዞች በዘርፉ ከተደራጁት ሁለት መቶ ማህበራት በስራ አፈጻጸማቸው እና ባላቸው ልምድ ሞዴል በመሆናቸው እንደተመረጡ በመግለጽ ድጋፉ በኮቪድ ወረርሽኝ እና በነበረው ጦርነት ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን የስራ እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃው ያላቸውን እምነት አንጸባርቀዋል:: የድጋፉ ተጠቃሚ ኢንተርፕራይዞችም ለተደረገላቸው የማቴሪያል ድጋፍ አመስግነው ቀደም ባሉት ጊዜያት በተቋሙ በተፈጠረላቸው የስራ እድል ተሳታፊ እንደነበሩ በማስታወስ በቀጠይም በሚፈጠሩ እድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና ተጨማሪ የሙያ እገዛ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል::