ወሎ ዩንቨርስቲ ከደረሰበት ውድመት በማገገም ከ6ሺ በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ።

ህዳር 4/2015 ዓ ም ወሎ ዩኒቨርሲቲ በደሴና ኮምቦልቻ ግቢዎች በተለያዩ ሙያዎች በመደበኛ፣ በርቀትና በክረምት መረሃ ግብር በመጀመሪያና ሁለተኛ ድግሪ ያሰለጠናቸውን 6308 ተማሪዎች ለ14ኛ ጊዜ አስመርቋል።
ከነዚህ ተመራቂዎች መካከል 1744 ሴቶች ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 4914ቱ በደሴ ግቢ የሰለጠኑ ሲሆን ቀሪዎቹ በኮምቦልቻ ግቢ የተሰለጠኑ ናቸው።

በዚህ የምርቃ ፕሮግራም ላይ የስራ መመሪያ ለተማሪዎች ያስተላለፉት የእለቱ የክብር እንግዳና የኢፌድሪ መከላከያ ሚኔስተር ሚኒስተር ዴኤታ ዶ/ር አህመድን መሀመድ ትምህርት በአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት የጎላ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ተመራቂዎች በተማራችሁበት መስኮች ያሉትን ተግዳሮቶች ገላልጣችሁ በማየት ለሀገራችን ሁለተናዊ እድገት የበኩላችሁን ሀላፊነት እንድትወጡ ሲሉ አሳስበዋል።

በተማሪዎች ምረቃ ፕሮግራም ላይ ሪፖርት ያቀረቡት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ በአለም አቀፍ የተከሰተውን የኮቪድ ወረርሽኝና የሰሜኑን ጦርነት ተቋቁመን ለምርቃ መብቃታችን የተቋማችን መምህራን፣ ሰራተኞችና ተማሪዎች የጋራ ስኬት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አያይዘውም ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሁሉም ኮሌጆች በሚባሉ መልኩ ከሀገር ውስጥና ውጭ ድርጅቶች ጋር አጋርነትን በመመስረት የተሻለ ድጋፍ ለማግኘት ተሰርቷል ብለዋል።

በመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ ዘመኑ እውቀት መር ዘመናዊ ቴክኖሎጂና ስራ ፈጣሪ ትውልድ የሚፈልግ በመሆኑ ተመራቂዎች ስራ ጠባቂ ሳይሆኑ ስራ ፈጣሪና ችግር ፈች እንድሆኑ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዚህ የምረቃ ፕሮግራን ወሎ ዩኒቨርሲቲ በግዕዝ ቋንቋ ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎችን አስመርቋል።

Scroll to Top