ወሎ ዩኒቨርሲቲ የአምባሰሏን ንግሥት የአርቲስት ማሪቱ ለገሰን የክብር ዶክተሬት አስረከበ

ወሎ ዩኒቨርሲቲ የአምባሰሏን ንግሥት የአርቲስት ማሪቱ ለገሰን የክብር ዶክተሬት አስረከበ

ጥር 4/2015 ዓ.ም (ወዩ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት)

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከተችው ለአምባሰሏ ንግሥት አርቲስት ማሪቱ ለገሰ በ2008 ዓ.ም ሰጥቷት የነበረውን የክብር ዶክትሬት ዛሬ አስረከበ።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በሥነሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት የወሎ ባህልና እሴት ጎልብቶ ለትውልድ እንዲተላለፍ ዩኒቨርሲቲው እየሰራ ነው። ለሀገር መሰረት የጣሉ ባለውለታዎችን በማክበር የክብር ዶክትሬት መስጠቱ ተተኪ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችን ለማፍራት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

አርቲስት ማሪቱ ለገሰ ወሎን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ከማስተዋወቅ ባለፈ ለኢትዮጵያውያን አንድነት ጉልህ ሚና በመጫወቷ የክብር ዶክትሬት መስጠቱን ተናግረዋል።

ለዚህም የዩኒቨርስቲው ሴኔት ሰኔ 2008 ዓ.ም የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ለመስጠት ወስኖ እንደነበር አስታውሰው፤ በወቅቱ ሀገር ውስጥ ባለመኖሯ ምክንያት ዛሬ እንዲሰጣት ተደርጓል ብለዋል።

አርቲስት ማሪቱ ለገሰ በበኩሏ ለተሰጣት ክብር አመስግና ስራዋን አጠናክራ ለመቀጠል ብርታት እንደሚሆናት ገልጻለች ። አክላም ከ23 ዓመታት የውጪ ሀገር ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ስትመለስ የኢትዮጵያ ህዝብ ላደረገላት አቀባበልና ለሰጣት ክብርም አመስግናለች።

አርቲስቷ፣ የአምባሰሏ ንግሥት፣ የቅኝቶች እናት፣ የባህል ሙዚቃ ንግሥት፣ ማሬዋ የሚሉና ሌሎች ቅጥያ ስሞችንም አግኝታለች።

በክብር ዶክትሬት አሰጣጡ ስነስርዓት ላይ የመቅደላና የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች፣ የደቡብ ወሎና የደሴ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ የቀድሞ ባልደረቦቿ፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የሴኔት አባላት፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ክብርና ምስጋና ለክብርት ዶክተር አርቲስት ማሪቱ ለገሰ ይሁን!!

Scroll to Top