የጦርነት ጉዳትን የተረዱ የማህበረሰብ ተቋማትን ግጭት ፈችነት አቅምን ማጎልበቻ (Empowering Trauma Informed Response Group in Preventing Social conflict) ስልጠና እና የትግበራ መርሃ ግብር ማጠናቀቂያ ውይይት ተካሄደ፡፡

ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም (ወሎ ዩኒቨርሲቲ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት)
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የልጅ ኢያሱ የሠላም፣ የዴሞክራሲ እና ልማት ምርምር ኢንስቲቱት ባለቤትነት እና በ USAID/OTI የገንዘብ ድጋፍ ላለፉት 7 ወራት በኮምቦልቻና በወረኢሉ ከተሞች ሲካሄድ የነበረው የጦርነት ጉዳትን የተረዱ የማህበረሰብ ተቋማትን ግጭት ፈችነት አቅምን ማጎልበቻ ስልጠና እና የትግበራ መርሃ ግብር መጠናቀቅን አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ የተገኙት ሲሆን ፕሮጀክቱ በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁን አመስግነው ለተሳታፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ የምስራቅ አማራ የUSAID/OTI አስተባባሪ አቶ ዳንዔል አሰፋም እንዲሁ ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈው የሁለቱ ተቋማት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽናግሌዎች ችግሮችን ተቋቁሞ የሚሻገር ማኅበረሰብን የመገንባት ስራ አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩት በሁለቱ ከተሞች ባለፉት 7 ወራት በስልጠና፣ በወርክሾፕ፣ በጎዳና ላይ የሰላም ንቅናቄ፣ በማህበረሰብ ንቅናቄ፣ በመንደር ውይይት እና በግጭት አፈታት ንቅናቄ ተሳታፊ የነበሩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ተወካዮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶች ማኅበራት፣ ወጣቶች፣ የሠላም ኮሚቴዎች እና የዕድር ተወካዮች ነበሩ፡፡

ውይይቱ በሥፋት ያተኮረው የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ በቀረበ ሪፖርት ላይ እና የማሕበረሰብ ተወካዮች ወደፊት ሥራቸውን አጠናክረው ሥለሚቀጥሉበት ሁኔታ ነበር፡፡ በተለይ በሁለቱም ከተሞች ግጭቶችን በመፍታትና ቀድሞ በመከላከል ያስገኙት ውጤትና ያገኙት ልምድ እጅግ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፎላቸዋል፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የልጅ ኢያሱ የሠላም፣ የዴሞክራሲ እና ልማት ምርምር ኢንስቲቱት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ተስፋዬ የሁለቱንም ከተሞች የሥራ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን የሁለቱ ከተሞች ተወካዮችም ያገኟቸውን ጥሩ ልምዶችና ተግዳሮቶች ለተሰብሳቢው አቅርበዋል፡፡ በጋራ ውይይቱም ወደፊት እንዴት መስራት እንዳለባቸው አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡

Scroll to Top