የእንስሳት ህክምና ሙያ ማሻሻያና አቅም ግንባታ ስልጠና ፕሮጀክት ከአንድ ጤና አንፃር ይፋ ተደረገ፡፡

ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም (ወሎ ዩኒቨርሲቲ ህ/ግ/ዳይሬክተር)

ወሎ ዩኒቨርሲቲ ጣሊያን ሀገር ከሚገኘው የቦሎኛ ዩኒቨርሲቲ፣ ቬት ፎር አፍረካ እና አፍሮሁን ኢትዮጵያ ከሚባሉ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የእንስሳት ህክምና ሙያ ማሻሻያ እና አቅም ግንባታ ስልጠና ፕሮጀክት በተዘጋጀ የመርሃ ግብር ትውውቅና ስልጠና ተጀምሯል፡፡

የእንስሳት ሃብት ልማቱ ዘርፍ ካገራችን የግብርና ምርት 40%፣ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት 20% ድርሻ አለው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሰፊ ሃብት የሚጠበቀውን ያህል ተጠቃሚ እንዳንሆን የእንስሳት በሽታ፣ የመኖ እጥረት፣ ባህላዊ እርባታ ዘዴ፣ የተቀናጀ የዝርያ ማሻሻያ ዘዴ አለመኖር፣ ዘመናዊ የእንስሳት ተዋፅኦ ማቀነባበሪያ ውስንነት እና የፖሊሲ ትግበራ ችግሮች ማነቆዎች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህም በላይ 70% እና በላይ የሚሆነው የሰዎች በሽታ የሚመነጩት ከእንስሳትና ከእንስሳት ተዋፅኦ ነው፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ችግሮቹን ፈትቶ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ከግብረ ሰናድ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የእንስሳት ህክምና ሙያ ማሻሻያ እና የአቅም ግንባታ ስልጠና ፕሮጀክት ከአንድ ጤና አንጻር ነድፎ ስራውን ጀምሯል፡፡

ስልጠናው ከለጋሽ ድርጅቶች በተገኘ ከ3.2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚከናወን ሲሆን 8 ፓኬጆች እንዳሉት ታውቋል፡፡ ስልጠናው የሚሰጠው በዘርፉ የካበተ ልምድ ባላቸው 13 ጣሊያናዊ ፕሮፌሰሮችና የአገር ውስጥ ምሁራን ሲሆን ከ500 በላይ የእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ባለሙያዎች ተሳትፊ ይሆናሉ፡፡

በፕሮጀክቱ ትውውቅ ላይ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ የተገኙ ስሆን ከጣሊያን አገር የመጡ የዘርፉ ምሁራንና ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ከማለታቸውም በተጨማሪ የዘርፉን አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡ በእለቱ የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ ዶ/ር አብዱ ሁሴን፣ የደሴ ከተማ ም/ከንቲባ እና የደሴ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰይድ የሱፍ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አህመድ በዕለቱ ተገኝተው መልዕክት አስተላለፈዋ፡፡

የእንስሳት ህክምና ት/ቤት ዲን ዶ/ር ታረቀኝ ትንታጉም አጠቃላይ ፕሮጀክቱን በተመለከተ አጭር ገለጻ አድርገዋል፡፡

Scroll to Top