የስነሰብዕ (Anthropology) ትምህርት ክፍል ከ4 መቶ በላይ የተለያዩ መጽሐፎችን በድጋፍ አገኘ

ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም (ወሎ ዩኒቨርሲቲ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት)

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሥነሰብዕ ትምህርት ክፍል ዋጋቸው ከ5 መቶ ሽህ ብር በላይ የሚገመቱ የማጣቀሻ እና የምርምር መጽሐፎችን ከዶ/ር ተፈሪ አባተ በስጦታ አግኝቷል፡፡

ዶ/ር ተፈሪ አባተ አሜሪካን አገር በሚገኘው የል ዩኒቨርሲቲ (Yale University) በሙያቸው መምህርና ተመራማሪ ሲሆኑ ከአሜሪካን መንግስት ባገኙት full-bright scholarship በዩኒቨርሲቲችን በስነሰብዕ ትምህርት ክፍል የተዛመደ የስራ ባልደረባ (affiliated staff) ሆነው በመምህርነት፣ በተመራማሪነትና የ2ኛ ዲግሪ የሥነሰብዕ ተማሪዎችን በማማከር ላይ ይገኛሉ፡፡

ዶ/ር ተፈሪ አባተ ከሁለተኛ ዲግሪያቸው ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች ያሰባሰቧቸውን የተመረጡ፣ በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉ፣ ለማህበራዊና ሰብአዊ ሳይንስ ኮሌጅ (ለአንትሮፖሎጅ፣ ሶስዮሎጂ ለቋንቋና ስነ-ጽሁፍ፣ ለፎክሎር፣ ለምርምር እና ለሌሎችም የትምህርት አይነቶች) ለመምህራንና ለተማሪዎች አጋዥ መጽሃፍትን ለአንትሮፖሎጅ ትምህርት ክፍል አስረክበዋል። ዶ/ር ተፈሪ አባተ በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት ካደረጉት ድጋፍ ባሻገር በወሎ ዩኒቨርሲቲ የወሎ ኢትኖግራፊክ ማዕከል (Wollo ethnographic records center) ተቋቁሞ የታለመለት አላማ እስኪሳካ ያለመሰልቸት ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ዶ/ር የሚያምረው ጆርጊ የሶሻል ሳይንስ ት/ቤት ዲን እንደገለጹልን ዶ/ር ተፈሪ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከኖርዌ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር ዓለማቀፍ ግንኙነት እና ትብብር እንዲኖረው፣ የኖርዌ የሥሰብዕ ምሁራን ወደ ወሎ ዩኒቨርሲቲ እንዲመጡ በማድረግ ወሎ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመበትን አካባቢ የመጠናት አቅም በማስረዳትና በማሳመን ከፍተኛ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደረጉ ምሁር እንደሆኑ ገልጸውልናል፡፡

ዲኑ አክለውም የሥነሰብዕ ትምህርት ክፍል አንዱ የምርምር ተግባር አቅጣጫ የህዝቡን ወግ፣ ባህል፣ ልምድና አኗኗር ሊያንጸባርቁና ሊገልጹ የሚችሉ የተለያዩ መጽሃፍትን፣ ጥናታዊ ጽሁፎችና ሌሎች ለጥናትና ምርምር የሚያግዙትን ቁሳቁሶችን ወደ አንድ ማዕከል በማሰባስብ ማከማቸትና ማደራጀት በመሆኑ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የኢትኖግራፊክ ሪከርድ ማዕከል ለማቋቋም አቅዶ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህም በመሆኑ ይህን የመጀመሪያ የማሰባሰብ ምእራፍ ተግባራዊ ለማደረግ የሚያግዝ ፈር ቀዳጅ ተግባር በማድግ በኩል ዶ/ር ተፈሪ አባተ የመጀመሪያው መሆናቸውን ዶ/ር የሚያምረው ተናግረው ለአደረጉት ድጋፍ በትምህርት ክፍሉ እና በት/ቤቱ ስም ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይም በውጭም ሆነ በሃገር ውስጥ በምናደርገው የማሰባሰብና የማደራጀት ስምሪት ዶ/ር ተፈሪ አባተ ከዩኒቨርሲቲው ጎን እንደሚሆኑና ከፍተኛ አስተዋጸኦ እንደሚያበርክቱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

Scroll to Top