ወሎ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ። ( የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት)

መስከረም 16/2015 ዓ ም የወሎ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት
የትምህርት ሚኔስተር የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንድሰጥ መወሰኑን ተከትሎ የወሎ ዩኒቨርሲቲ አራት የመፈተኛ ቦታዎችን ማዘጋጀቱን ገልጿል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ እንደገለጹት ተፈታኞች በሀገር አቀፍ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት ፈተናቸውን እንድወስዱ በደሴ በዋናው ግቢና በመምህራን ኮሌጅ እንድሁም በኮምቦልቻ ደግሞ በቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩቱና በኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅ ሙሉ ዝግጅት ተደርጓል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ለተፈታኞች አገልግሎት የሚሰጡ የመኝታ፣ የመመገቢያና የመፈተኛ ክፍሎች በጥንቃቄ የተዘጋጁ እንደሆነ አብራርተዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከ34,200 በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለማስፈተን ሙሉ ዝግጅት ያደረገ ሲሆን በተለይም ወደ ደሴ የሚመጡ ተማሪዎች ከአየር ንብረቱ ጋር የሚስማማ አልባሳትን እንድጠቀሙ ዩኒቨርሲቲው አሳስቧል።
የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና በሁለት ዙር የሚሰጥ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ዩኒቨርሲቲው ከ18 ሺ በላይ ተማሪዎች በሁለተኛ ዙር ደግሞ ከ15 ሺ በላይ እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል።

Scroll to Top