ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከ3.3 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጭ 43 ሺህ ደብተርና ከ36ሺ በላይ እስኪርቢቶ ድጋፍ አደረገ።
ደሴ-መስከረም 14/2015 ዓ.ም/ደሴ ፋና/ዩኒቨርሲቲው በክረምቱ በደቡብ ወሎ ዞን፣ በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞንና በደሴ ከተማ የሚገኙና የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ከ9-12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ሲሰጥ የቆየው ስልጠናም ውጤታማ እንደነበር ተገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው በወራሪ ቡድኑ የደረሰበት ውድመት ከባድና ራሱን በማቋቋም ላይ የሚገኝ ቢሆንም በወቅቱ ባለው የዋጋ ንረት ምክንያት በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌትነት መላከ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊትም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ለትምህርት ስራው እገዛ አድርጓል ብለዋል።
ድጋፉ ለደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ዋግህምራ ፣ ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞኖች፣ ለደሴ ከተማ፣ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ማህበርና ለተለያዩ በአካባቢው የሚገኙ ት/ቤቶች ተደርጓል።
የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረጀ አማረ በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት በርካታ የዞኑ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ እንዳይሆኑ ጥረት እየተደረገ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ በወሳኝ ወቅት የተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የዋግ ልማት ማህበር ስራ አመራር ቦርድ ም/ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር መልሰው ተፈራ በበኩላቸው ወሎ ዩኒቨርሲቲው ለዋግህምራ ዞን ከዚህ በፊትም ለጤናና ትምህርት ተቋማት ድጋፍ ማድረጉንና የህብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ ያደረገው ጥረት ጉልህ ነበር ብለዋል።
ድጋፉን የተረቡት የትምህርት ተቋማት ሀላፊዎችና ተወካዮች ዩኒቨርሰቲው ያደረገው ድጋፍ ለሌሎች ተቋማትም አርአያ ሲሆን ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ድጋፉን የዩኒቨርስቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ አስረክበዋል።
በሌላ በኩል ዩኒቨርስቲው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ከ9-12 ክፍል ላሉ ተማሪዎች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ውጤታማ እንደነበር የዩኒቨርስቲው የማህበረሰብ አገልግሎትና ስልጠና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ጉግሳ ተናግረዋል።
250 የሚሆኑ ተማሪዎች በስልጠናው የተሳተፉ ሲሆን የተሻለ ትኩረት ሊሰጣቸው በሚገቡ የትምህርት አይነቶች ፣ የህይወት ክህሎት፣ የማነቃቂያ እና በቤተ ሙከራ የታገዙ ስልጠናዎች ሲሰጡ ቆይተዋል።
ከዚህ በፊትም በESTEEM መርሀ ግብር ታቅፈው የነበሩ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የፕሮግራሙን ስኬታማነት አስመስክረዋል።
ዩኒቨርስቲው ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ተፈታኞች የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን ያነሱት ዳይሬክተሩ ይህም የዩኒቨርስቲው መምህራንና የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች መምህራን የተሳተፉበት ነበር ብለዋል።
ለዚህም ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው እየሰጠ ያለውን የማህበረሰብ አገልግሎት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ዶ/ር ጌታቸው ተናግረዋል።

