ወሎ ዩኒቨርሲቲ እየተራቆተ ያለውን የሎጎ ሀይቅ ወደ ነበረበት ለመመለስ እየሰራ ነው።

መስከረም 17/2015 ዓ ም (ወሎ ዩኒቨርሲቲ ህዝብ ግንኙነት)፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስተር ጋር በመተባበር እየተራቆተ የመጣውን የሎጎ ሀይቅ ወደነበረበት ለመመለስ ባለፉት ሶስት አመታት ጥናቶችን ሲያካሄድ ቆይቷል።

ዩኒቨርሲቲው በጥናቱ እየቀነሰ የመጣውን የሀይቁን የውሃ መጠንና የአሳ ምርት ለመጨመር አማራጭ የጥናት ውጤቶችን ይፋ አድርጓል።

በተለይም ዩኒቨርሲቲው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ የመጣውን የአሳ ሀብት በዘላቂነት መፍትሄ ለመስጠት ዘላቂ ማህበረሰብ ተኮር የአሳ ሀብት አጠቃቀምና አማራጭ የማስገሪያ ቦታዎችን እንድጠቀሙ ለሚመለከታቸው አካላት ስልጠናዎችን ሰጥቷል።

በስልጠናው ላይ የተገኙት የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ ዩኒቨርሲቲው የሎጎንና አርዲቦ ሀይቆችን ለመታደግ አስፈላጊ የሆኑ የፕሮጀክት እቅዶችን በማካተት የውሃ መጠኑንና የአሳ ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በሎጎ ሀይቅ ላይ ምርምር እያካሄዱ ያሉት ዶ/ር አሰፋ ተሰማ የሎጎ ሀይቅን ለመታደግ ሀይቁን ከደለል መከላከል፣ የደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድን ማሻሻል፣ የሎጎ ሐይቅን ደጀን/ Buffer zone/ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው እጽዋተቶች ማለትም እንደ ማንጎ፤አቮካዶ፤ሙዝ መሸፈንና የሐይቁን ተፋሰስ የአንቀርቀሃ ወንዝን መሰረት ያደረገ ሥነ-ሕይወታዊ ዘዴ መጠቀም ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራቶች ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

የሀይቁን የአሳ ምርት ወደነበረበት መመለስ ከተፈለገ ወደ ሀይቁ የሚገባውን የፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መታደል አዳነ ገልጸዋል።

በሎጎ ሀይቅ ላይ ስለሚሰራው ስራ ዶ/ር አሰፋ ተሰማ ገላጻ ያደረጉ ሲሆን ትኩረት ከሚሰጥባቸው ጉዳዬች ውስጥ ደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ሎጎ ሀይቅ ከተለቀቀ የሚያሳድረው ተፅኖ ላይ ስልጠና የሰጡት ዶ/ር መታደል አዳነ ሲሆኑ የደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ አያያይዝ እና አወጋገድ ትኩረት ሰጥተው አብራርተዋል።

የአሳ ሀብት አጠቃቀም ባለሙያ የሆኑት አቶ አደም ሙሃመድ በበኩላቸው በአሳ አሰጋገር ላይ ያተኮረ ስልጠና ከሰጡ በኋላ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ሀይሉ ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይቶችን በማካሄድ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።

በመጨረሻም የወሎ ዪኒቨርስቲ የልማትና አለም አቀፍ ግንኙነት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አጸደ ተፈራ ወሎ ዬኒቨርስቲ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን ብዙ ስራወችን እንደሚሰራ በመዝጊያ ንግግራቸው ገልጸዋል።

Scroll to Top