ወሎ ዩኒቨርሲቲ በካናዳ አገር ከሚገኘው ግሎባል ኤይድ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለቦሩ ሜዳ እና ኮን ሆስፒታሎች የህክምና መገልገያ እቃዎችንና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ::

ነሐሴ 5/2014 ዓ.ም (ወ.ዩ. ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት)

በሀገራችን ኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል በተካሄደው ጦርነት 11.9 ቢሊዮን ብር የሚገመት ውድመት የደረሰበት ወሎ ዩኒቨርሲቲ ተቋሙን መልሶ ለመገንባት ባቋቋመው የመልሶ ግንባታና ሃብት አፈላላጊ ኮሚቴ አማካኝነት ካናዳ ሀገር ከሚገኘው ግሎባል ኤይድ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ግማሽ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የህክምና መገልገያ እቃዎችንና ቁሳቁሶችን ለቦሩ ሜዳ እና ኮን ሆስፒታሎች ፍጋፍ አደረገ።

በድጋፍ ርክክቡ ላይ የወሎ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የግሎባል ኤይድ ኢትዮጵያ እና የሁለቱ ሆስፒታሎች ተወካዮች፣ ከደቡብ ወሎ ዞን እና ከደሴ ከተማ የመጡ የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ የህክምና ተቋማትን መልሶ በመገንባት ዙሪያ የትብብር ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል በኩል በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ ዩኒቨርስቲያችን ላይ የደረሰውን መጠነ ሰፊ ጉዳት መልሶ ለመገንባት ጠንካራ ኮሚቴ አቋቁመን እየሰራን ሲሆን ለህብረተሰባችን የህክምና አገልግሎት ለተማሪዎቻችን ደግሞ የተግባር ትምህርት ማግኛ የሆኑ በአካባቢያችን ያሉ ሆስፒታሎችን መልሶ በማቋቋም በኩልም ድጋፎችን በማሰባሰብ ላይ እንገኛለን ብለዋል። ይህ ድጋፍም ባለፈው ለደሴ አጠቃላይ ሆስፒታል ከተደረገው ድጋፍ የቀጠለ መሆኑን ገልጸው ግሎባል ኤይድ ኢትዮጵያ ለህብረተሰባችን አጋርነቱን በማሳየት አብሮን እየሰራ ስላለ ምስጋናችንን እናቀርባለን ሲሉ ተናግረዋል.

የግሎባል ኤይድ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጌታቸው ደማም በበኩላቸው ድርጅቱ የተመሰረተው ለወገን ደራሽ ወገን ነው በሚል መርህ ስለሆነ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በመሰባሰብ ለሀገራችን እና ለወገናችን ለመድረስ የቻልነውን እያደረግን እንገኛለን ብለዋል፤ ሀገራችንን ማገልገል ግዴታችን እና ብድራችንን እንደመመለስ ጭምር ነው ያሉት ዶክተር ጌታቸው ወሎ አካባቢ ላይ ላሉት የህክምና ተቋማት በወሎ ዩኒቨርሲቲ በኩል ድጋፍ እያደረግን ነው፣ እኛ እዚህ የተገኜነው ደግሞ ይሄን ድጋፍ ለማስረከብ ብቻ ሳይሆን በዚህ ጦርነት ምክንያት በወገናችን እና በሀገራችን ላይ የደረሰውን ጥፋት ገምግመን ቀጣይ ስራዎችን ለመስራት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሊ መኮንን እና የደሴ ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይድ የሱፍ የተደረገውን ድጋፍ አስመልክተው መልእክት ያሰተላለፉ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት ህብረተሰባችን እና የአገልግሎት መስጫ ተቋማቶቻችን ላይ ከፍተኛ ውድመት፣ ዝርፊያ እና ምዝበራ ተካሂዷል ነገር ግን በእንደዚህ አይነት መተባበር በበለጠ ቁጭትና ተስፋ ተቋማቶችን መልሰን እያደራጀን፣ ህዝባችንንም ወደቀደመ ሰላሙ እንዲመለስ በትጋት እንሰራለን ለተደረገው ድጋፍም ታላቅ ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል።

Scroll to Top