ወሎ ዩኒቨርሲቲ ለአካል ጉዳተኛ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ አገር አቀፍ ተፈታኞች የአካል ጉዳት ድጋፍ ቁሳቁሶችን በስጦታ አበረከተ፡፡

ጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም (ወዩ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት)

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያው ዙር 17 ሺህ የሚጠጉት የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎችን ተቀብሎ በአራት የፈተና ጣቢያዎች ሲያስፈትን ቆይቶ በሠላም አጠናቋል፡፡ ከነዚህ ተማሪዎች ውስጥ የአካል ጉዳት ያለባቸው ተፈታኞች እንደነበሩ የሚታወቅ ሲሆን ዩኒቨርሲቲያችን ይህንኑ ጉዳታቸውን ታሳቢ ያደረገ ቅድመ ዝግጅት በማድረጉ ተማሪዎቹ ያለምንም እንከን ፈተናቸውን እንዲወስዱ አድርጓል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ችግር በማስተዋል የዩኒቨርሲቲው ማናጅመንት በወሰነው መሰረት ከ93 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸውን ዊልቸርና ነጭ ብትር በመግዛት 33 ለሚሆኑ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የአካል ድጋፍ ቁሳቁሶች ሰጥቷል፡፡

የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎቹ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናው አካል ጉዳተኞች ታሳቢ ተደርጎ በዩኒቨርሲቲ መሰጠቱ ተረጋግተው መፈተን እንደቻሉ የገለጹ ሲሆን ወሎ ዩኒቨርሲቲም ላደረገላቸው እርዳታ አመስግነዋል፡፡

ድጋፉ ከተደረገላቸው ተፈታኞች መካከል ተማሪ እንድሪስ አብዱ በሰጠው አስተያየት፤ ከዚህ በፊት በየትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሲወስዱ በሚፈለገው ልክ አካል ጉዳተኛን ታሳቢ ያደረገ ቅደመ ዝግጅትና እንክብካቤ እንዳልነበር አስታውሶ ዘንድሮ ግን ፈተናው በዩኒቨርሲቲ መሰጠቱና አካል ጉዳተኛን ታሳቢ ያደረገ ቅደመ ዝግጅት መደረጉ በጥሩ ስሜት ተረጋግቶ እንዲፈተን እድል እንደሰጠው፣ ለመፈተኛ ክፍል፣ ለምግብ ቤት፣ ለክሊኒክና ለሌሎችም አማካኝ ቦታ ላይ መኝታ ክፍል ተመቻችቶለት ችግር ካጋጠመውም በፍጥነት እንዲፈታለት ተንከባካቢ ተመድቦለት በደስታ እንደተፈተነ አስረድቷል፡፡ ዊልቸርም ማግኘቱ የረጅም ጊዜ ጥያቄው መልስ እንዲያገኝና ድካምን እንዲቀንስለት እንዳስቻለው ተናግሯል።

በሌላ በኩል ማየት የተሳናቸውም ተፈታኞች የተረጋጋና በሳል ሰው ተመድቦላቸው በተደጋጋሚ በሚፈልጉት ልክ ረጋ ብለው የሚያነቡላቸው ፈታኞች በማግኘታቸው ፈተናውን መስራት እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡ ለተደረገላቸው የነጭ ብትር ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ በበኩላቸው፤ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በስኬት እንዲጠናቀቅ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ጭምር ቅድመ ዝጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ለምግብ ቤት፣ ለመፈተኛ ክፍል፣ ለክሊኒክና ለሌሎችም ማህበራዊ መገልገያዎች አማካኝና ምቹ ሁኔታ ላይ መኝታ ክፍል ተመቻችቶላቸው በጥሩ ስሜትና በደስታ ፈተናውን እንዲወስዱ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡

Scroll to Top