አይካፕ-ኢትዮጵያ (ICAP-ETHIOPIA) ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ስለወባ በሽታ ህክምና ስልጠና እየሰጠ ነው

ግንቦት 22 ቀን 2015 ዓ.ም (ወሎ ዩኒቨርሲቲ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት)

አይካፕ-ኢትዮጵያ (ICAP-ETHIOPIA) ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ስለወባ በሽታ ህክምና (Comprehensive Malaria Case Management) ለህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለተመራቂ ሀኪሞች እና የጤና መኮንን ተማሪዎች እየተሰጠ ነው፡፡

በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መታደል አዳነ ስልጠናው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በአገር አቀፍ ደረጃ ወባን ከኢትዮጵያ በ2023 ዓ.ም በማጥፋት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ያለመ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዘርፉ ብቁ ባለሙያ ለማፍራት ያለመ መሆኑን ገልጸው ከስልጠናው በኋላ ሰልጣኞች ጥሩ የወባ በሽታ ህክምና እውቀት እንደሚኖራቸውና በሙያው ውጤታማ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር መታደል አያይዘውም ስልጠናው ለሁሉም የ2015 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎች የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው በመጀመሪያው ዙር ከግንቦት 21-25, 2015 ዓ.ም በቀጣይ ዙርም ደግሞ ለሌሎች ተመራቂ የጤና ተማሪዎች እንደሚሰጥ አሳውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል የICAP-ETHIOPIA/PMI ተወካይ የሆኑት አቶ አለሙ አለባቸው በበኩላቸው ስልጠናው በተለያዩ ባለሙያዎች፣ ብዙ ልምድ ባላቸው አሰልጣኞች በንድፈሃሳብና በተግባር ተደገፎ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ በቅድመ ስልጠና ምዘና ተጀምሮ በድኅረ ስልጠና ምዘና እንደሚጠናቀቅ አስገንዝበዋል፡፡ በተጨማሪም የስልጠናው ሙሉ ወጪ በICAP-ETHIOPIA ፕሮጀክት የሚሸፈን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስልጠናውን የወሎ የኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን በሲኔር ሀኪም ዶ/ር መንግስተአብ ኃይሉ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ማስተዋል አረፋይኔ፣ መ/ር ታደሰ ገ/እግዚአብሔር፣ መ/ር ልዑል መኮንን እንዲሁም የብዙ ጊዜ ልምድ ባላቸው የአይካፕ-ኢትዮጵያ አሰልጣኞች እና ሌሎች በወባ ፕሮግራም ልምድ ባላችው ሀኪሞችና ባለሙያዎች እየተሰጠ ነው፡፡ በዚህ ስልጠና 58 ተመራቂ የህክምና ዶክተሮች እና 34 የጤና መኮንኖች በአጠቃላይ በመጀመሪያው ዙር ለ92 ተመራቂ ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

Scroll to Top