ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቴ 23/09/2015 ዓ.ም
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በ2015 ዓ.ም በሚሰጠው የተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
መውጫ ፈተናን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ የመውጫ ፈተና የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ተማሪዎችን በማብቃት ፈተናውን እንዲያልፉ በሚደረገው ጥረት ከተቋሙ ባሻገር የትምህርት ከፍሎች እና መምህራን ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ከጦርነቱ በኋላ በመልሶ ግንባታ ያከናወናቸው ልዩ ልዩ ተግባራት፣ ያሉን የልህቀት ማዕከላት፣ የገነባናቸው ላቦራቶሪና ወርክሾፖች ውጤት የሚለካው የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እንዲያልፉ ማድረግ ሲቻል መሆኑን አስምረውበታል፡፡
ከማነጅመንት አባላት አንስቶ እስከ ትምህርት ክፍል ሃላፊዎች ድረስ በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ከሚገኙ አካላት ጋር በነበረው የውይይት ጊዜ ሞጂውል በማዘጋጀት፣ ቱቶሪያል በመስጠት፣ ቴክኖሎጂውን በማለማመድ እና ሞዴል ፈተና በመስጠት እስካሁን በተሰራው የቅድመ ዝግጅት ስራ እና እስከፈተናው ቀን ድረስ ሊሰሩ ይገባል በተባሉ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል፤ ከመድረክም ገንቢ ሃሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡
ከውይይቱ በፊት እና በኋላ በነበረው ጊዜ ተሳታፊዎች ኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆን በተቋሙ ውስጥ በመሰራት ላይ ስላሉ ፕሮጀክቶች፣ ላቦራቶሮዎች፣ ወርክሾፖች እና ትሪትመንት ፕላንት በሳይንቲፊክ ዳይሬክተሩ በዶ/ር መላኩ ታመነ እና በሚመለከታቸው ባለሙያዎች ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
