በአማራ ክልል የእንሰት ዝርያን ለማላመድ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከአጋር አካላት ጋር እየሰራ ነው።

በአማራ ክልል የእንሰት ዝርያን ለማላመድ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከአጋር አካላት ጋር እየሰራ ነው።

ጥቅምት 25 ቀን 2915 ዓ.ም (ወዩ ህ/ግንኙነት ዳይሬክተር)

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ የባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት፣ ከምርምር ማዕከላት፣ ከደሴ ቲሹ ካልቸር፣ ከወልድያና መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን የእንሰት ዝርያን የማላመድና የማስፋፋት ስራ እየተሰራ ነው።

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በኩታበር፣ በስሪንቃ፣ በሀርቡና ጃሪ እያካሄደ ያለውን የእንሰት ዝርያ የማላመድ እና የማስፋፋት እንቅስቃሴ ከአጋርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የመስክ ምልከታ አካሄዷል። በዚህ የመስክ ምልከታ የእንሰት ሰብልን ከማሳ እስከ ምሳ በሚል ፕሮግራም ማህበረሰቡ ሰብሉን እንዴት መጠቀም እንደሚችል በተግባር የማሳየት ስራ ተሰርቷል።

በተለይም በኩታበር የእንሰት ሰብልን ለምግብነት እንዴት ማዘጋጀት እንደሚቻል በተካሄደው እንቅስቃሴ የአካባቢው አርሶ አደሮች እንሰትን እስከዛሬ አለመጠቀማቸው ቁጭትን ፈጥሮባቸዋል።

በፕሮግራሙ የተሳተፉት የኩታበር ወረዳ አርሶ አደሮች የእንሰት ሰብልን በስፋት ለመጠቀም የወሎ ዩኒቨርሲቲና አጋር አካላት ዝርያውን የማስፋፋትና የማላመድ ስራ በስፋት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አወል ሰይድ ዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂውን የማሳየትና የማላመድ ስራ ከሰራ አርሶ አደሮችና የግብርና ተቋማት የማስፋፋት ስራውን ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል። አያይዘውም አርሶ አደሮችና የግብርና ተቋማት ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥም ዩኒቨርሲቲው የማገዝ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለቀጣዮቹ 5 አመታት ከወሎ ዩኒቨርሲቲና አጋር አካላት ጋር በመተባበር በየአመቱ 1000 (አንድ ሺ) የእንሰት ዝርያዎችን በአማራ ክልል ለማላመድና ለማስፋፋት እየሰራ ይገኛል።

Scroll to Top