ሐምሌ 28/ 2014 ዓ.ም (ወ.ዩ. ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት)
ከተለያዩ ወረዳዎች እና ከደሴ ከተማ ለተውጣጡ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ የESTEM (English, Science, Technology, Engineering and Mathematics) ተማሪዎች በለውጥ እና ስብእና ግንባታ ላይ ያተኮረ የማነቃቂያ ስልጠና በወሎ ዩኒቨርሲቲ ደሴ ግቢ ተሰጠ።
ስልጠናውን የወሰዱት ተማሪዎች ከደቡብ ወሎና ኦሮሚያ ልዩ ዞን እንዲሁም ከደሴ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ እና በወሎ ዩኒቨርሲቲ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት የሚሰጣቸው ተማሪዎች ናቸው። ይህ ስልጠና የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስ ልማትና ዓለም አቀፍ ግንኑነት ም/ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ከተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን ሰልጣኝ ተማሪዎቹ ከወረዳዎቻቸውና ከከተማ አስተዳደሩ ካሉ ትምህርት ቤቶች መካከል አብላጫ ውጤት በማምጣት ተመልምለው በወሎ ዩኒቨርሲቲ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት የሚወስዱ ናቸው።
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን እናንተን የምናሰለጥነውና የክረምት ትምህርት በዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች እየተማራችሁ ክረምቱን እንድታሳልፉ የምናደርገው ለኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይሆን ለአለም ዩኒቨርሲቲዎች ማዘጋጀት ስለምንፈልግ ነው፤ ከ10 እና 15 ዓመት በኋላ ሀገራችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚኖራት ቦታ በእናንተ የሚወሰን ይሆናል፤ ስለሆነም ይህ የለውጥና የመልካም ስብዕና ግንባታ ስልጠና ክረምቱን እኛ ጋር ስትቆዩ በዩኒቨርሲቲው አስተማሪዎቻችን ከምትቀስሙት ትምህርት ጋር ተዋህዶ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣፈንታ ላይ ትልቅ አበርክቶ ያላችሁ እንድትሆኑ መሰረት ይሆናችኋል ሲሉ ገልጸዋል።
አያይዘውም መጭው ጊዜ አለም በሳይንስ፣ በኮምፕዩተር ኮዲንግ፣ በሂሳብ፣ በፊዚክስና በቋንቋ ልህቀት ላይ የተቆራኜ ስለሚሆን አሁን በምታገኙት ትምህርትና ስልጠና በእነዚህ ትምህርቶች ጎበዞች በመሆን የማሰብና የማሰላሰል አቅማችሁን በማሳደግ ለራሳችሁ፣ ለቤተሰባችሁ፣ ለሀገራችሁና ለአለም የምትተርፉ ለመሆን ጠንክራችሁ እንድትማሩ አደራ እላችኋለሁ ሲሉ ተናግረዋል።
ስልጠናዎቹ በተለያዩ ርእሶች ላይ የተሰጡ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አማረ ምትኩ፣ መምህር ሙሉዬ ታረቀኝ እና መምህር በውቀቱ ዘለቀ ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ እንዲሁም መምህር ተስፋዬ ለገሰ ከስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ስልጠናውን ሰጥተዋል