ለወሎ ዩኒቨርሲቲ አንስቴዢያ ትምህርት ክፍል የእውቅና ኘሮግራም ተዘጋጀ

ነሐሴ 5/2014 ዓ.ም (ወ.ዩ. ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጽ/ቤት)

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአንስቴዢያ ትምህርት ክፍል ላለፉት ተከታታይ አመታት የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ላስመዘገበው ውጤት የእውቅና ፕሮግራም ተዘጋጀ።

የእውቅና ፕሮግራሙ የተዘጋጀው በሀገር አቀፍ የብቃት መመዘኛ ፈተና (National Licensure Examination) የወሰዱ የትምህርት ክፍሉ ተመራቂ ተማሪዎችን ሙሉ በሙሉ በማሳለፍ አመርቂ ውጤት እንዲያመጡ በማድረጉ ነው። በፕሮግራሙ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃን አስማሜ፣ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መታደል አዳነ፣ የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ልኡል መስፍን፣ የኮሌጁ የስራና ትምህርት አመራሮች እና የትምህርት ክፍሉ መምህራን ተገኝተዋል።

ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶችና ለፕሮግራሙ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መታደል አዳነ በተመዘገበው ስኬት መደሰታቸውን ገልፀው በኮሌጁ ውስጥ ባሉ ሌሎች ትምህርት ክፍሎች የአንስቴዠያ ትምህርት ክፍልን ተሞክሮ በመዉሰድ ለውጤት እንዲበቁ ጠይቀዉ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች ተመርቀዉ ሲወጡ ከሰው ህይወት ጋር ቀጥታ ስለሚገናኙ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለትምህርት ጥራት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን በትጋት እንሰራለን ብለዋል።

የአንስቴዠያ ትምህርት ክፍል ተሞክሮን ለፕሮግራሙ ታዳሚዎች ያቀረቡት የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ረ/ፕ ሷሊህ መሃመድ ውጤታማ የሆኑባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ያቀረቡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ስርዓተ-ትምህርቱን በአግባቡ ወደ ተግባር በመለወጥ፣ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ትምህርትን አጣምሮ በመስጠት፣ ያለውን መጠነኛ የማስተማሪያ ግብዓት በአግባቡ በመጠቀም፣ አዳዲስ የማስተማሪያና የመመዘኛ መንገዶችን በመጠቀም፣ በትምህርት ክፍሉ ውስጥ የተለያዩ አስተባበሪዎችና ኮሚቴዎችን በመጠቀም በትጋት በመስራት እንዲሁም የዲፖርትመንቱ መምህራንና ተማሪዎች በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚጠብቅባቸውን በመወጣታቸው የመጣ ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ልኡል መስፍን በአንስቴዥያ ትምህርት ክፍል የተገኜውን ውጤት አድንቀው ወሎ ዩኒቨርስቲ ከመቸውም በላይ ከሆስፒታሉ ጋር በትብብር እየሰራ እንደሆነና ለወደፊትም በጋራ የተሻሉ ስኬቶችን ማስመዝገብ እንደሚቻል ገልጸዋል። የኮሌጁ የትምህርት ጥራትና ተቋማዊ ለውጥ አስተባባሪ ረ/ፕ ተናኘወርቅ ድልነሳ በበኩላቸው ይህ የእውቅና ፕሮግራም የተዘጋጀው ለስኬት የበቁትን ለማበረታታትና ለማመሰገን እንዲሁም በሌሎች የትምህርት ክፍሎች በመልካም ተሞክሮነት እንዲወሰድ በማሰብ ነው ብለዋል። በዚሁ መሰረት ለዚህ የተቀናጀ ተግባርና አመርቂ ውጤት ጉልህ አስተዋጽ ለነበራቸው የወሎ ዩኒቨርሲቲና ደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአንስቴዢያ ትምህርት ክፍሎች፤ በሁለቱም ተቋማት ለሚሰሩ አንስቴቲስቶች እንዲሁም ለደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በተመዘገበው ትልቅ ውጤት መደሰታቸውን ገልጸው በሃገራችን ተከስቶ በነበረው ጦርነት ማግስት ትምህርት ክፍሉ ያስፈተናቸውን ተማሪዎች 100% ማሳለፍ መቻሉ የሚደነቅ ተግባር በመሆኑ ለዚህ ስኬት የበቃበትን ተሞክሮዎች ከኮሌጁ ባለፈ በዩኒቨርሲቲው ደረጃ የልምድ ልውውጥ ሊደረግበት የሚገባ ነው፤ ወደፊትም የዩኒቨርሲቲውን በጀት ለኮሌጆችና ለትምህርት ክፍሎች በማከፋፈል ብቻ ለውጥና ጥራት ስለማናመጣ እንደዚህ አይነት ውጤታማነትን መሰረት ያደረጉ ድጋፎችን፣ በተለይም አለም ዓቀፍ የትምህርትና የምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት የሚያደርጉትን ይበልጥ እናበረታታለን በማለት አሁን ለተገኜው አኩሪ ውጤት አስተዋጽኦ ላደረጉ የዩኒቨርሲቲውና የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ ዲኖች፣ አስተባባሪዎች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና መምህራን ምስጋና አቅርበዋል።

Scroll to Top